Sunday, September 27, 2015

ከቁምሳጥኑ በር በስተጀርባ


       ሁል ጊዜ ከእናቴ ጋር ቲቪ ወይም የሆነ ፊልም ነገር ስናይ ፍቅረኛሞች እጅ ለእጅ ሲያያዙ ወይም ሲሳሳሙ (ወይም ምንም አይነት የፍቅር አገላለፅ ሲሰጣጡ) በድንጋጤ ብዛት ልቤ ከእግሬ በታች ወርዶ ይመለስና ሰማዩ ተሰባብሮ፣ ምድሪቷ አፏን ከፍታ፣ ሕይወት ሚባል ነገር ከነጭራሹ ቢቀር እያልኩ እማፀን ነበር፤ ፍቅረኛሞቹ ፆታቸው ተመሳሳይ ከሆነ። ልሳኔ ተነፍንፎ ልክ እንደ አብዛኛው አይድል መጀመሪያ ዙር ተወዳዳሪ፣ ለዛሬም ሆነ ለነገ እንደማይሳካልኝ እያወኩኝ፣ ከእናቴ አንደበት ሚወጣውን የጥላቻ ዝማሬ ለማቀንቀን እሞክር ነበር። ትላንት ማታ ግን ከእናቴ ጋር 'How to Get Away with Murder' እያየን ዋናዋ ተዋናይ Viola Davis ከ Famke Janssen ከንፈር ለከንፈር ገጥመው ሲሳሳሙ እናቴ ያለችው አስግርሞኝ ክትክት ብዬ ሳኩኝ። በዛን ቅስበት ያን የፍርሃት ስሜት ላስታውሰው እንኳን አልቻልኩም። እራሴን ለእናቴ ይፋ ማድረጌ ምን ያህል ነፃ እንዳረግኝ የተረዳሁት ከዛ በኋላ ነው። ሳስበው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን የሚያውቁ ሰዎች ሰለ ጉዳዩ የጥላቻ ንግግር ቢጀምሩ አይደለም የነርሱን ሀሳብ እያስተጋባው ላወራ ይቅርና ከከንፈራቸው ሌላ ቃል እስኪወጣ መጠብቅ ምችል አይመስለኝም።  

       እራስን ይፋ ማድረግ (Coming out (ከዚ የተሻለ አማርኛ ትርጓሜ ላገኝ አልቻልኩም!)) ማለት የሆነ ከባድ ንግግርን ማድረግ ነው። ይህ ንግግር ከምናደርገው ሰው ጋር ያለን ቅርበት ንግግሩን ከባድ ወይም ቀላል ያደርገዋል። ግን ከሁሉም ከባድ፣ ነገር-ግን ወሳኝ የሆነው ከራሳችን ጋር ምናደርገው ንግግር ነው። ራስን (ማንነትን) ፍለጋ በራሱ አዳግች እና ማለቂያ የሌለው ነው (የኛ ህብረተሰብ ደግሞ አንድ ሰው የወሲብ ፍላጎቱ ትንሽ ለየት ካለ የዛን ሰው ማንነት በዛ ውስጥ ብቻ ነው ሚያዩት )። ቁልፉ ነገር ግን ማንነታችንን ከሌሎች ሰዎች አለመፈለግ ወይም በሌሎች ሰዎች አስተሳሰብ ላይ አለመገንባት ነው፣ ምክንያቱም ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ አስተያየት አለው እና የሁሉኑም ሰው ፍላጎት ማስተናገድ አይቻልም። ሳይንስ እንደሚለው የሰው ፍጡር ስነ-ግብር  በጣም ውስብስብ የሆነ እና እንደየሰዉ ሚለያይ ነገር ነው።  ስለዚህም ትኩረታችንን ውስጣችን ሚሰማን ስሜት ላይ ነው ማድረግ ያለብን። ለመጀመሪያ ጊዜ ወንድ ሆኖ ለወንድ መማረክ ምን እንደሆነ (ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ/ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አንፃር) ካስተዋልኩበት ቀን ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ "ወደፊት ሁሉም በጎ ይሆናል" እያልኩ ራሴን ማፅናናት እስከጀመርኩበት ጊዜ ብዙ ቀናት እና ብዙ ክስተቶች አልፈዋል።  በነዚያ ጊዜያት ውስጥ በአብዛኛው ሚሰማኝ ፍርሃት ነበር። ነገርግን ፍርሃቴን ለጥርጣሬዎቼ መልስ ከማግኘት እንዲከለክለኝ እጅ አልሰጠውትም። 

       የተመሳሳይ ፆት አፍቃሪ መሆኔን ከመናገሬ በፊት አንዳንድ ጓደኞቼ ስለ ጉዳዩ ያላቸው አስተያየት  ጥሩ አልነበረም። ነገር ግን እውነታውን ሲረዱ አስተያየታቸው በመጠኑ ተሻሸሏል። ለዚህም ምክንያት ሊሆን ሚችሉ ሁለት ነጥቦች አሉ፤ ስለጉዳዩ ጥሩ አመለካከት ቢያንፀባርቁ ሌሎች ሰዎች ሚሰጡትን ምላሽ ፈርተው ግን እውነታውን ሲረዱ ለኔ ያላቸው ፍቅር ከሌሎች ሰዎች አሉባልታ ስለሚያስበልጡ ፤ ወይም ደግሞ በቅርብ ሚያውቁት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ስለሌለ ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በአውምሯቸው የሳሉት የተዛባ አስተያየት በኔ ምክንያት ተሸርሽሮ  እውነታውን መረዳት ሰለቻሉ ነው። ያም ሆነ ይህ ዋናው ቁም ነገር ያስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱ ነው።

ይህ ማለት ግን በየሰዉ በር እየሄድኩኝ "መልካሙን ዜና ሰማችሁ? ወንድ የሚያፈቅር ወንድ ነኝ!"  ማለት አለብኝ አይደለም። እስካሁን ጌይ መሆኔን ማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ።  በተጨማሪ ደግሞ ይፋ ከመውጣታት በፊት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።  የሰዎች ምላሽ መጥፎ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች የገዛ ልጆቻቸውን ከቤት ያባርራሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተመሳሳ ፆታ አፍቃሪ መህን በህግ ያስቀጣል። አሳዛኙ እውነታ እርሱ ነው፤ ኢትዮጵያ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ወጥቶ ለመኖር ያን ያህል አመቺ አይደለችም ፤ ነገር ግን ይህን ሁኔታ ለመቀየር ደግሞ ሰዎች ደፍረው ወጥተው መኖር አለባቸው። 

በ ጁን 26 2015 እ.እ.እ  በአሜሪካ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅረኛሞች የጋብቻ መብት ሲከበር ፕሬዚዳንት ኦባማ የሰጠው ንግግር መቼም አይረሳኝም። 
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃርዎች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰው ነን ። የኢትዮጵያውያን ልጆች ፣ ወላጆች፣ እህቶች፣ ወንድሞች፣ ጓደኞች ወዘተ ነን። ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን እውነታ አልተገነዘቡም። ምናልባት ይህን እውነታ እንዲገነዘቡ ማድረግ የኛ ስራ ይሆን? 

Thursday, July 30, 2015

ኢትዮጲያ ለምን ዜጎቿን ትጠላለች?

NY Pride 2015
ባለ ብዙ ሺህ ዘመን ባህል እና ቅርስ ሃገር ናት፤ ኢትዮጵያ። ለዚህም ነው በኢትዮጵያዊነቴ ትልቅ ኩራት ያለኝ። ነገር ግን በሃገሬ ውስጥ 'በኩራት' ይቅርና 'በሰላም' መኖር አልችልም፤ ወንድ ሚያፈቅር ወንድ ስለሆንኩኝ። ባለፈው አመታዊ Pride በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው የተሳተፉ ወጣቶችን በተመለከተ ብዙ ሰዎች የሰጡትን ምላሽ አይቼ ነበር። አብዛኛው የጥላቻ እና የክፋት ዛቻ ነበር። ግን ከመናደድ ይልቅ ለምን ይህ ሁሉ ጥላቻ መጣ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።

"ሃገራችንን አትበክሉ!!!"
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ሲሉ ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ምን አይነት ስዕል በአይምሮአቸው እንደሚስሉ ማሰብ ይከብደኛል። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን እንደ ጉንፋን ሚጋባ ይመስላቸዋል እናም በማህበራዊ ተቃውሞ ወይም በጥላቻ ሚወገድ ይመስል ደፋ ቀና ሲሉ ይታያል። ኢትዮጲያ ውስጥ ህዝቡ ስለጉዳዩ አስተያየቱን ቢቀይር እና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት ቢከበር እርግጠኛ ነኝ ብዙ ሰዎች ከተደበቁበት ወጥተው ማንነታቸውን ይፋ አድርገው ይኖራሉ። ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ይህ የሚመስላቸው የጌይ መብት መከበር ጌይ ያልሆኑ ሰዎችን ጭምር ጌይ ሆነው ይፋ እንዲወጡ ሚገፋፋ ነው። ምን ?!?!? በተያያዘ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የተመሳሳይ  ፆታ አፍቃሪዎችን መብት ሚደግፍ ሁሉ ያው እርሱም ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነው ብለው ያስባሉ (ባይሆንም እንኳ)።
እንደዚህ ከሆነ የጥቁሮችን መብት የሚደግፍ ነጭ ጥቁር ነው?! የእንስሳትን መብት የሚደግፍ ሰው ማስክ ያጠለቀ ድመት ነው?!
ለመሆኑ ሃገርን መበከል ምን ማለት ነው?  አንደ አንዳንድ ሃገሮች በጦርነት እና በአጥፍቶ-ጠፊዎች ሰላምን ማጣት ነው?  በረሃብ እና በድርቅ መረሸን? ሰው ሁሉ ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን አጥቶ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሲነዳ ነው? ነው ወይስ እንደ ሶዶም እና ጎሞራ በእሳት ናዳ ከምድረ-ገፅ ስንትጠፋ ነው? እንደ Othello በቅናት ተነሳሽነት ካልሆነ በቀር አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ፍቅር ምክንያት አጥፍቶ ጠፊ ሊሆን ሚችል አይመስለኝም። ይሉቁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዲሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብት ረገጣ የበለጠ አጥፍቶ-ጠፊዎችን ይፈጥራል ብዬ እገመታለው። አሁን ስለ ፖለቲካ ብዙ ማለት ባልፈልግም ይህን እላለው፣ ኢትዮጵያ መበከል ከጀመረች 24 አመታት አልፏታል ። 
ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች በአንድ አገር ውስጥ በነፃነት ስለኖሩ አይድለም ድርቅ እና ረሃብ ሚነሳው። ኋላቀር የግብርና ዘይቤ፣ ከመጠን በላይ የሆነ የሰው ቁጥር፣ እና ማይረባ የኢኮኖሚያዊ ፖሊስ ለድርቅ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት ስለተከበረ አንደ ሶዶም እና ጎሞራ ኢትዮጵያ አትጠፋም። ቤልጂየም ከ 12 ዓመት በፊት፣ ካናዳ ከ 10 ዓመት  በፊት፣ ኔዘርላንድ  ከ 15 ዓመት በፊት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የጋብቻ መብት የሰብአዊ መብት መሆኑን አገናዝበው በሕግ አፅድቀውት አስካሁን አንዲት የእሳት ናዳ ከሰማይ ወርዶ ሳይነካቸው አሉ። በጠቅላላው  "አገሬን አትበክሉ" ሚሉ ሰዎች ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ያላቸው ግንዛቤ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ለዚህም እንደምክንያትነት ምቆጥረው  1 - ብዙ ጊዜ ሀበሾች ስንባል ስለአንድ ነገር "ለምን?" ብሎ ከመመራመር ይልቅ የሰው ወሬ ማስተጋባት ይቀለነላል። 2 - በሕወታቸው ውስጥ በይፋ ወቶ የሚኖር ዜጋ የለም (ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ከልብ ሚወዱት/ሚያከብሩት ታዋቂ ሰው)። ምናልባት በቅርብ ምያውቁት ዜጋ የሆነ ሰው ቢኖር ኖሮ፣ ምናልባት የተቅበዘበዘ ሃሳብ ከማስተጋባት ይልቅ ከምር ለመረዳት ይሞክሩ ይሆናል፣ ምናልባት። 

ነገርግን እንደዚህ አይነት "ሃይማኖት አጥባቂ" ሰዎች ባሉበት (ከዚህ የባሱ አስፈሪ ምላሾች አሉ) ሀገር ውስጥ በይፋ ወጥቶ መኖር ለሕይወት አስጊ ነው። ስለ ሌሎች ሃይማኖቶች ብዙ ማውቀው ነገር የለም ግን በክርስትና ሃይማኖት የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር "እግዜር ስለማይፈቅድ" በክፉኛ ነው ሚጠላው (ምንም እንኳ ሌሎች ሰው ደንታ ማይሰጣቸው እግዜር ማይፈቅዳቸው ብዙ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም)። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሃይማኖተኞች ኢትዮጵያን "ከግብረ-ሶዶም የፀዳች" እንድትሆን ሚችልቱን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው (የዜጎችን ሰብአዊ መብት እስከመጣስ ድረስ)። ያለምንም ጥርጥር ማንኛውም ሰው የፈለገውን አይነት እምነት የመከተል /አለመከተል መብት እንዳለው አምናለው። እንዲሁም ደግሞ ሐይማኖት ለኢትዮጵያ / ለዓለም ያበረከተውን አስተዋፅኦ አውቃለው (ስነ-ጥበብ፣ ኪነ-ጥበብ ፣ ፖለቲካ፣ ወዘተ )። ነገርግን አሁኑ ባለንበት ክፍለዘመን እንደማህበረሰብ እና እንደ ሐገር ለሚያጋትሙን ውስብስብ ችግሮች "እግዜር ያውቃል"፣ "እግዜር ስላለ ነው"፣ ወይም  "እግዜር አይፈቅድም" ማለት አጥጋቢ መልስ አይድለም። ምናልባት ለአንድ ክርስቲያን አጥጋቢ መልስ ሊሆን ይችላል። ለ 9 ሚሊዮን ሰዎች ግን አንደ መልስ ሊቆጠርም አይገባም። ለምሳሌ አንድ ኦርቶዶክስ ሐይማኖት  ተከታይ ለገና ፆም ሥጋ አለመብላት መብቱ ነው። ነገርግን የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ ሰው በመላ አብሮኝ መፆም አለበት፣ ሃይማኖቴ ሰለማይፈቅድ ስጋ ሲበላ ወይም ስጋ  መብላትን ሲደግፍ የተገኘ ይታሰር እና ኢትዮጵያዊነቱን ይነጠቅ ማለት በጭራሽ አይችልም። በተመሳሳይ መልክ ሃይማኖትን መሳሪያ አድርጎ የሰውን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ማጥቃት  ለአይምሮዬ ምንም አየገባውም። የህን ሊረዳ ማይችል ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ ካለ፣ "ከግብረ-ሶዶም የፀዳች ኢትዮጵያ!" የሚለው መዝሙር ከISIS "ከክርስትያኖች የፀዳች ዓለም" ነጠላ ዜማ ወይም ከ አዶልፍ ሂትለር "ከ አይሁድ ዘር የፀዳች ዓለም" ከተሰኘው አልበም በምን ይለያል?


Saturday, June 20, 2015

5 ስለ ግብረ-ሶዶማዊነት ("homosexual lifestyle") የተዛቡ ንግግሮች እና እውነታው

ከልጅነቴ ጀምሮ እኚን እና እንደኚ ያሉ ሌሎች ተመሳሳይ ሀሳቦች ስለ ግብረ-ሶዶማዊነት ሲወሩ ሰምቻለው። ግን ከብዙ ጥናት እና የራሴ የኑሮ ልምድ በኋላ እውነታውን ለመረዳት ችያለው። ከነዚህ ሀሳቦች ዋና ዋና ያልኳቸው አምስቱ እኚህ ናቸው። (ጥሩ የአማርኛ ቃል ስላጠረኝ "ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ" ለማለት "ግብረ-ሶዶሜያዊ" የሚለውን ቃል ተጠቅሜአለው።)

1 - "ኢሠብዓዊ እና ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ተግባር ነው"

ብዙ ጊዜ ይህን ሃሳብ ለማሳመን አንዳንድ ጥያቄዎቸን ይሰነዝራሉ። "የግብረ-ሥጋ ግኑኝነት ዓላማ ልጅ መውለድ ከሆነ ግብረ-ሶዶማዊያን ለምን ልጅ አይወልዱም?"፣ "ግብረ-ሶዶማዊነት በሰዎች ላይ እንጂ በሌሎች እንስሳት ላይ የት አለ?" ፣ "እንዴት ሊሆን ይችላል?"።
የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ዓላማ ልጅ መውለድ አይደለም! ዓላማው ያ ቢሆን ኖሮ በዚ ዓለም ላይ ሚወለዱ ህፃናት ቁጥር  በዚ ዓለም ላይ በወንድ እና በሴት መሃል ከሚደረግ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ቁጥር በላይ ይሆን ነብር፤ እውነታው ግን ያ አይደለም። በርግጥ ልጅ መውለድ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት አንድ ውጤት ነው፤ ነገር ግን አንድን ሰው ከ ሌላ ሰው ጋር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ለመፈፀም የሚገፋፋው ዘሩን ተክቶ ለማይት፣ ወልዶ ለመሣም፣ ወይም 'አይኑን በአይኑ ለማየት' ሳይሆን ከውስጥ የሚመነጭ የወሲብ ጥማትን ለማርካት ነው። በኢትዮጲያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት እንደ ነውር እንጂ እንደ የሰው-ተፈጥⶂዊ-ባህሪ ተደርጎ ስለማይታይ ይህን እውነታ ሰዎች አይገነዘቡትም።
ግብረ-ሶዶማዊነት ከሰው ዘር ውጪ በ ሌሎች እንስሳቶች ላይ ይታያል!!!!
ምንም እንኳን የሰው DNA ውስጥ የዛን ሰው ወሲባዊ ፍላጎት(sexual orientation) ሚቆጣጠር GENE ባይኖርም ሌሎች Epigenetic marks በእርግዝና ጊዜ እና ከወሊድ በኋላ የዛ ሰው GENE እንዴት እንደሚሰራ ይቆጣጠራሉ። እኚህ Epigenetic marks በእርግዝና ጊዜ የሆርሞን መጠን መዛባት ምክንያት ይከሰታሉ። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው ግብረ-ሶዶማዊ ሆኖ ሊወለድ ይችላል

2 - "በፀሎት እና  በልምምድ ከግብረ-ሶዶማዊነት መላቀቅ ይቻላል"

ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ጌይ ሆኜ ይህንን ስፅፍ አልገኝም ነበር። 10ኛ ክፍል እያለው 'ሮዝ' መጽሄት ስለ 'ግብረ-ሶዶማዊነት' ዘግበው ነበር። በዘገባውም ውስጥ ሌሎች ጌይ የሆኑ ሰዎች ታሪካቸውን በትንሹ አጋርተው ነብር። በዚህም ጊዜ ነው ስለራሴ ማንነት የተገነዘብኩት። ግን ይህ ግንዛቤ ያመራኝ ወደ ጭንቀት እና ፍርሃት ነብር። ታድያ እንደ ማንኛውም ክርስቲያን በፍርሃት ጊዜ ወደ ፈጣር ዞርኩኝ። ፆም ፣ ፀሎት ፣ ስግደት ፣ ጥምቀት ፣ ቅዳሴ ፣ ሰምበት ትምህርት ፤ ምንም ለውጥ። በመጨረሻ ፈጣሪዬ እኔን ከመቀዬሙ የተነሳ ከዚ ህይውት ሊያድነኝም እንኳ ፈቃደኛ ያልሆነ ነበር የመሰለኝ። ህይወቴን ከመጥላቴ የተነሳ ህይውትን ሚያሳምሯት ትናንሽ ደስታዎችን እንኳ መጎንጨት አቃተኝ። ያጋጠመኝን መጥፎ አጋጣሚ ሁሉ 'ከፈጣሪ የወረድ የሚገባኝ ቅጣት ነው' እያልኩ አይምሮዬ ውስጥ በፈጠርኩት ትንሽ ሲዖል ስነድ ነብር። እርግጠነኛ ነኝ እኔ ብቻ አይድለሁም በእንዲህ አይነት አግጣሚ ውስጥ ያለፍኩት። ለዚያውም በቅርብ ማውቀው የነበረ ልጅ እራሱን እጥፍቷል (6ኛ ክፍል ተማሪ ነብር መርዝ ጠትቶ ሲሞት)። በርግጥ ግብረ-ሶዶማዊነት ሐጥያት ነው(በአንዳንድ ሐይማኖቶች መሰረት)፤ ግን ሐጥያት የሌለበት ማን ነው? ሐጥያት የሌለበት ካለ የመጀመሪያውን ስድብ ይሰንዝር!

3 - "ወደ ግብረ-ሶዶማዊነት የገባኸው  . . . . .  ስለሆነ ነው"

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚሰጡት መላምት በጣም ያስቃል። "ትንሽ ሆነህ ተደፍረህ ስለነብር ነው"፤ በህይወቴ የወሲብ ጥቃት ደርሶብኝ አይውቅም። አንድ ወንድ (ጌይ ቢሆንም እንኳ) የውሲብ ጥቃት ቢደርስበት፣ ያንን ጥቁር ቀን ስለሚያስታውሰው ወሲብ የተባለ ከነጭራሹ ያስጠላዋል እንጂ የበለጠ እንዲወደው አያደርገውም። "ከእናትህ ጋር ብቻ (ያለ አባት) ስላድግ ነው"፤"ያደግክበት አካባቢ ተሰጠዖ ነው"፤ ለብዙ ጊዜ ይህ እውነት ይመስለኝ ነብር፣ ነገር ግን ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ታናሽ ወንድሜም ጌይ ይሆን ነብር። ሁለታችንም ያለአባት ከአንድ አይነት እናት ጋር፣ አንድ አይነት ትምህርት ቤት ውስጥ፣ እና አንድ አይነት ቤት/ሰፍር ውስጥ አንድ አይነት ምግብ እየበላን ነው ያደግነው ግን እኔ ብቻ ነኝ ግይ። ለምን?  ከሁሉም ሚገርመኝ ግን "ግብረ-ሶዶማዊ የሆንከው አጉል ዘመናዊ ለመሆን ፈልገህ ስለመረጥክ ነው" ሚለው ነው። ምርጫ ቢኖረኝ ኖሮ በብቸኝነት ግራተጋብቶ መሰቃይትን፣ በዘመድ በጎረቤት በወላጅ ... በሐገር መጠላትን፣ በእስር እና በሞት መቀጠታትን (ብዙ አፍሪካዊ አገሮች ውስጥ ግብረ-ሶዶማዊነት በህግ ያስቀጣል) ለምን ብዬ እመርጣለው??  ከላይ እንድጠቀስኩት ግብረ-ሶዶማዊነትን መለውጥ አይቻልም፤ እንደዝያውም ደግሞ አንድ ሰው ጌይ ሆኖ ሳይወለድ ጌይ መሆን አይችልም። ይህንን ማመን ለሚያቅጣቸው መልሴ ቀላል ነው "ለ1 ቀን ጌይ ሁኑ እና ወደነበራችሁበት ተመልሳቹህ አሳዩኝ!"

4 - "ግብረ-ሶዶማዊያን = የወሲብ አጥቂዎች"

ማንኛውም አይነት የወሲብ ጥቃት ሊገፀፅ እና ሊወገድ የሚገባ ተግባር ነው። በተለይም በንፁሃን ህፃናት ለይ የሚፈፀም የወሲብ ጥቃት በጣም አሰቃቂ ነው። በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚደርሱት የወሲብ ጥቃቶች ውስጥ 38.5%  ህፃናት ላይ ነው። ከነዚህም ውስጥ 68 % ጥቃቶች የሚደርሱት ህፃናቱ በሚያውቋቸው ሰዎች ሲሆን 29% በህፃናቱ ዘመዶች ነው። እዚህጋ ማለት የፈለጉት ማንኛውም ሰው የወሲብ አጥቂ ወይም ተጠቂ ሊሆን ይችላል። የወሲብ ጥቃት የወሲብ ጥቃት ነው ። አንደኛው ከሌላኛው ሚያስበልጠው ወይም የሚያሳንሰው ነገር የለም። በተጨማሪ ደግሞ ግብረ-ሶዶሟዊነት እና የወሲብ አጥቂነትን ሚያገናኝ ምንም ነገር የለም። አንድ ሰው ገና ለገና ጌይ ስለሆነ በዚች ዓለም ላይ ያለ ወንድ በሙሉ (ዘር ፣ እድሜ ፣ ቀለም ፣ ቁመት ፣ ፀባይ ፣ ሐብት ፣ የትምህርት ደረጃ .... ወዘተ ሳይለይ) ይማርከዋል ማለት አይደለም (በወሲብ አይን ማየት ይቅርና)። 

5 - "ግብረ-ሶዶማዊነት የወሲብ እና የአይምሮ በሽታ ያስከትላል"
ማንኛውም የሆነ ልቅ ግብረ-ስጋ ግኑኝነት ያባላዘር በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም ጌይ ወንዶች በ ኤድስ እና በሌሎች የአባላዘር በሽታዎች የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው።  ምክንያቱም ባዬሎጂ እንደሚያስረዳው የሰው ፊንጢጣ የተሰራው በጣም ስስ ከሆነ ቲሹ ሰለሆነ በቀላሉ ሊሰነጠቅ እና በሽታ ሊያስተላልፍ ይችላል። ግን ይህ ኮንዶም በመጠቀም በቀላሉ ሊውገድ ይችላል ። በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የኤድስ ወረርሽኝ አለ፤ በተለይ በጌይ ወንዶች መሐል። ተለያዩ ፀረ-ኤድስ አካሎች ቢኖሩም ጌይ ለሆኑ ሰዎች ምንም አይነት እርዳታ አይሰጡም። ይህም የሆነው ሐገሩ (መንግስት) በሚደግፈው ጥላቻ ምክንያት ነው። ስለዚህ ችግሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በግብረ-ሶዶማውያን ላይ የሚያተኩር ጸረ ኤድስ እና ሌሎች የጤና ተቋሞች አለመኖር ነው እንጂ ግብረ-ሶዶማውያን ሰለሆኑ አይደለም።
አንድአንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዝ ግብረ-ሶዶሜያውያን ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ለእይምሮ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ይህም የሚከሰተው ከህብረተሰብ በሚመጣ ትልቅ ግለት እና ማንቋሸሽ ነው። አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ በሙሉ ሲንቁአሸሽ ፣ ሲሰደብ ፣ ሲደበደብ ወዘተ በዓውምሮው ላይ ትልቅ ተጽአኖ ያመጣል። በተጨማሪ ደግሞ ሚሰማቸውን ስሜት ጨፍልቀው ፤ እንደሌላው ተመሳስለው ለመኖር ሲሞክሩ ወይም ደግሞ እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቅው ሁለት ህይወት (Doubel life)  ለለመኖር ሲሞክሩ ፣ በጭንቀት እና ባለመረጋጋት አይምሮአቸውን ያሳብዳሉ። ነገሮች ካልተቀየሩላቸው ይህ ሁኔታ ወደ ባሰ የአይምሮበችምሽታ ወይም እራሳቸውን እንዲያጠፉ ይገፋፋቸዋል።