Sunday, September 27, 2015

ከቁምሳጥኑ በር በስተጀርባ


       ሁል ጊዜ ከእናቴ ጋር ቲቪ ወይም የሆነ ፊልም ነገር ስናይ ፍቅረኛሞች እጅ ለእጅ ሲያያዙ ወይም ሲሳሳሙ (ወይም ምንም አይነት የፍቅር አገላለፅ ሲሰጣጡ) በድንጋጤ ብዛት ልቤ ከእግሬ በታች ወርዶ ይመለስና ሰማዩ ተሰባብሮ፣ ምድሪቷ አፏን ከፍታ፣ ሕይወት ሚባል ነገር ከነጭራሹ ቢቀር እያልኩ እማፀን ነበር፤ ፍቅረኛሞቹ ፆታቸው ተመሳሳይ ከሆነ። ልሳኔ ተነፍንፎ ልክ እንደ አብዛኛው አይድል መጀመሪያ ዙር ተወዳዳሪ፣ ለዛሬም ሆነ ለነገ እንደማይሳካልኝ እያወኩኝ፣ ከእናቴ አንደበት ሚወጣውን የጥላቻ ዝማሬ ለማቀንቀን እሞክር ነበር። ትላንት ማታ ግን ከእናቴ ጋር 'How to Get Away with Murder' እያየን ዋናዋ ተዋናይ Viola Davis ከ Famke Janssen ከንፈር ለከንፈር ገጥመው ሲሳሳሙ እናቴ ያለችው አስግርሞኝ ክትክት ብዬ ሳኩኝ። በዛን ቅስበት ያን የፍርሃት ስሜት ላስታውሰው እንኳን አልቻልኩም። እራሴን ለእናቴ ይፋ ማድረጌ ምን ያህል ነፃ እንዳረግኝ የተረዳሁት ከዛ በኋላ ነው። ሳስበው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን የሚያውቁ ሰዎች ሰለ ጉዳዩ የጥላቻ ንግግር ቢጀምሩ አይደለም የነርሱን ሀሳብ እያስተጋባው ላወራ ይቅርና ከከንፈራቸው ሌላ ቃል እስኪወጣ መጠብቅ ምችል አይመስለኝም።  

       እራስን ይፋ ማድረግ (Coming out (ከዚ የተሻለ አማርኛ ትርጓሜ ላገኝ አልቻልኩም!)) ማለት የሆነ ከባድ ንግግርን ማድረግ ነው። ይህ ንግግር ከምናደርገው ሰው ጋር ያለን ቅርበት ንግግሩን ከባድ ወይም ቀላል ያደርገዋል። ግን ከሁሉም ከባድ፣ ነገር-ግን ወሳኝ የሆነው ከራሳችን ጋር ምናደርገው ንግግር ነው። ራስን (ማንነትን) ፍለጋ በራሱ አዳግች እና ማለቂያ የሌለው ነው (የኛ ህብረተሰብ ደግሞ አንድ ሰው የወሲብ ፍላጎቱ ትንሽ ለየት ካለ የዛን ሰው ማንነት በዛ ውስጥ ብቻ ነው ሚያዩት )። ቁልፉ ነገር ግን ማንነታችንን ከሌሎች ሰዎች አለመፈለግ ወይም በሌሎች ሰዎች አስተሳሰብ ላይ አለመገንባት ነው፣ ምክንያቱም ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ አስተያየት አለው እና የሁሉኑም ሰው ፍላጎት ማስተናገድ አይቻልም። ሳይንስ እንደሚለው የሰው ፍጡር ስነ-ግብር  በጣም ውስብስብ የሆነ እና እንደየሰዉ ሚለያይ ነገር ነው።  ስለዚህም ትኩረታችንን ውስጣችን ሚሰማን ስሜት ላይ ነው ማድረግ ያለብን። ለመጀመሪያ ጊዜ ወንድ ሆኖ ለወንድ መማረክ ምን እንደሆነ (ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ/ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አንፃር) ካስተዋልኩበት ቀን ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ "ወደፊት ሁሉም በጎ ይሆናል" እያልኩ ራሴን ማፅናናት እስከጀመርኩበት ጊዜ ብዙ ቀናት እና ብዙ ክስተቶች አልፈዋል።  በነዚያ ጊዜያት ውስጥ በአብዛኛው ሚሰማኝ ፍርሃት ነበር። ነገርግን ፍርሃቴን ለጥርጣሬዎቼ መልስ ከማግኘት እንዲከለክለኝ እጅ አልሰጠውትም። 

       የተመሳሳይ ፆት አፍቃሪ መሆኔን ከመናገሬ በፊት አንዳንድ ጓደኞቼ ስለ ጉዳዩ ያላቸው አስተያየት  ጥሩ አልነበረም። ነገር ግን እውነታውን ሲረዱ አስተያየታቸው በመጠኑ ተሻሸሏል። ለዚህም ምክንያት ሊሆን ሚችሉ ሁለት ነጥቦች አሉ፤ ስለጉዳዩ ጥሩ አመለካከት ቢያንፀባርቁ ሌሎች ሰዎች ሚሰጡትን ምላሽ ፈርተው ግን እውነታውን ሲረዱ ለኔ ያላቸው ፍቅር ከሌሎች ሰዎች አሉባልታ ስለሚያስበልጡ ፤ ወይም ደግሞ በቅርብ ሚያውቁት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ስለሌለ ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በአውምሯቸው የሳሉት የተዛባ አስተያየት በኔ ምክንያት ተሸርሽሮ  እውነታውን መረዳት ሰለቻሉ ነው። ያም ሆነ ይህ ዋናው ቁም ነገር ያስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱ ነው።

ይህ ማለት ግን በየሰዉ በር እየሄድኩኝ "መልካሙን ዜና ሰማችሁ? ወንድ የሚያፈቅር ወንድ ነኝ!"  ማለት አለብኝ አይደለም። እስካሁን ጌይ መሆኔን ማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ።  በተጨማሪ ደግሞ ይፋ ከመውጣታት በፊት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።  የሰዎች ምላሽ መጥፎ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች የገዛ ልጆቻቸውን ከቤት ያባርራሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተመሳሳ ፆታ አፍቃሪ መህን በህግ ያስቀጣል። አሳዛኙ እውነታ እርሱ ነው፤ ኢትዮጵያ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ወጥቶ ለመኖር ያን ያህል አመቺ አይደለችም ፤ ነገር ግን ይህን ሁኔታ ለመቀየር ደግሞ ሰዎች ደፍረው ወጥተው መኖር አለባቸው። 

በ ጁን 26 2015 እ.እ.እ  በአሜሪካ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅረኛሞች የጋብቻ መብት ሲከበር ፕሬዚዳንት ኦባማ የሰጠው ንግግር መቼም አይረሳኝም። 
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃርዎች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰው ነን ። የኢትዮጵያውያን ልጆች ፣ ወላጆች፣ እህቶች፣ ወንድሞች፣ ጓደኞች ወዘተ ነን። ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን እውነታ አልተገነዘቡም። ምናልባት ይህን እውነታ እንዲገነዘቡ ማድረግ የኛ ስራ ይሆን? 

No comments:

Post a Comment