Thursday, July 30, 2015

ኢትዮጲያ ለምን ዜጎቿን ትጠላለች?

NY Pride 2015
ባለ ብዙ ሺህ ዘመን ባህል እና ቅርስ ሃገር ናት፤ ኢትዮጵያ። ለዚህም ነው በኢትዮጵያዊነቴ ትልቅ ኩራት ያለኝ። ነገር ግን በሃገሬ ውስጥ 'በኩራት' ይቅርና 'በሰላም' መኖር አልችልም፤ ወንድ ሚያፈቅር ወንድ ስለሆንኩኝ። ባለፈው አመታዊ Pride በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው የተሳተፉ ወጣቶችን በተመለከተ ብዙ ሰዎች የሰጡትን ምላሽ አይቼ ነበር። አብዛኛው የጥላቻ እና የክፋት ዛቻ ነበር። ግን ከመናደድ ይልቅ ለምን ይህ ሁሉ ጥላቻ መጣ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።

"ሃገራችንን አትበክሉ!!!"
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ሲሉ ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ምን አይነት ስዕል በአይምሮአቸው እንደሚስሉ ማሰብ ይከብደኛል። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን እንደ ጉንፋን ሚጋባ ይመስላቸዋል እናም በማህበራዊ ተቃውሞ ወይም በጥላቻ ሚወገድ ይመስል ደፋ ቀና ሲሉ ይታያል። ኢትዮጲያ ውስጥ ህዝቡ ስለጉዳዩ አስተያየቱን ቢቀይር እና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት ቢከበር እርግጠኛ ነኝ ብዙ ሰዎች ከተደበቁበት ወጥተው ማንነታቸውን ይፋ አድርገው ይኖራሉ። ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ይህ የሚመስላቸው የጌይ መብት መከበር ጌይ ያልሆኑ ሰዎችን ጭምር ጌይ ሆነው ይፋ እንዲወጡ ሚገፋፋ ነው። ምን ?!?!? በተያያዘ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የተመሳሳይ  ፆታ አፍቃሪዎችን መብት ሚደግፍ ሁሉ ያው እርሱም ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነው ብለው ያስባሉ (ባይሆንም እንኳ)።
እንደዚህ ከሆነ የጥቁሮችን መብት የሚደግፍ ነጭ ጥቁር ነው?! የእንስሳትን መብት የሚደግፍ ሰው ማስክ ያጠለቀ ድመት ነው?!
ለመሆኑ ሃገርን መበከል ምን ማለት ነው?  አንደ አንዳንድ ሃገሮች በጦርነት እና በአጥፍቶ-ጠፊዎች ሰላምን ማጣት ነው?  በረሃብ እና በድርቅ መረሸን? ሰው ሁሉ ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን አጥቶ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሲነዳ ነው? ነው ወይስ እንደ ሶዶም እና ጎሞራ በእሳት ናዳ ከምድረ-ገፅ ስንትጠፋ ነው? እንደ Othello በቅናት ተነሳሽነት ካልሆነ በቀር አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ፍቅር ምክንያት አጥፍቶ ጠፊ ሊሆን ሚችል አይመስለኝም። ይሉቁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዲሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብት ረገጣ የበለጠ አጥፍቶ-ጠፊዎችን ይፈጥራል ብዬ እገመታለው። አሁን ስለ ፖለቲካ ብዙ ማለት ባልፈልግም ይህን እላለው፣ ኢትዮጵያ መበከል ከጀመረች 24 አመታት አልፏታል ። 
ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች በአንድ አገር ውስጥ በነፃነት ስለኖሩ አይድለም ድርቅ እና ረሃብ ሚነሳው። ኋላቀር የግብርና ዘይቤ፣ ከመጠን በላይ የሆነ የሰው ቁጥር፣ እና ማይረባ የኢኮኖሚያዊ ፖሊስ ለድርቅ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት ስለተከበረ አንደ ሶዶም እና ጎሞራ ኢትዮጵያ አትጠፋም። ቤልጂየም ከ 12 ዓመት በፊት፣ ካናዳ ከ 10 ዓመት  በፊት፣ ኔዘርላንድ  ከ 15 ዓመት በፊት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የጋብቻ መብት የሰብአዊ መብት መሆኑን አገናዝበው በሕግ አፅድቀውት አስካሁን አንዲት የእሳት ናዳ ከሰማይ ወርዶ ሳይነካቸው አሉ። በጠቅላላው  "አገሬን አትበክሉ" ሚሉ ሰዎች ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ያላቸው ግንዛቤ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ለዚህም እንደምክንያትነት ምቆጥረው  1 - ብዙ ጊዜ ሀበሾች ስንባል ስለአንድ ነገር "ለምን?" ብሎ ከመመራመር ይልቅ የሰው ወሬ ማስተጋባት ይቀለነላል። 2 - በሕወታቸው ውስጥ በይፋ ወቶ የሚኖር ዜጋ የለም (ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ከልብ ሚወዱት/ሚያከብሩት ታዋቂ ሰው)። ምናልባት በቅርብ ምያውቁት ዜጋ የሆነ ሰው ቢኖር ኖሮ፣ ምናልባት የተቅበዘበዘ ሃሳብ ከማስተጋባት ይልቅ ከምር ለመረዳት ይሞክሩ ይሆናል፣ ምናልባት። 

ነገርግን እንደዚህ አይነት "ሃይማኖት አጥባቂ" ሰዎች ባሉበት (ከዚህ የባሱ አስፈሪ ምላሾች አሉ) ሀገር ውስጥ በይፋ ወጥቶ መኖር ለሕይወት አስጊ ነው። ስለ ሌሎች ሃይማኖቶች ብዙ ማውቀው ነገር የለም ግን በክርስትና ሃይማኖት የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር "እግዜር ስለማይፈቅድ" በክፉኛ ነው ሚጠላው (ምንም እንኳ ሌሎች ሰው ደንታ ማይሰጣቸው እግዜር ማይፈቅዳቸው ብዙ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም)። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሃይማኖተኞች ኢትዮጵያን "ከግብረ-ሶዶም የፀዳች" እንድትሆን ሚችልቱን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው (የዜጎችን ሰብአዊ መብት እስከመጣስ ድረስ)። ያለምንም ጥርጥር ማንኛውም ሰው የፈለገውን አይነት እምነት የመከተል /አለመከተል መብት እንዳለው አምናለው። እንዲሁም ደግሞ ሐይማኖት ለኢትዮጵያ / ለዓለም ያበረከተውን አስተዋፅኦ አውቃለው (ስነ-ጥበብ፣ ኪነ-ጥበብ ፣ ፖለቲካ፣ ወዘተ )። ነገርግን አሁኑ ባለንበት ክፍለዘመን እንደማህበረሰብ እና እንደ ሐገር ለሚያጋትሙን ውስብስብ ችግሮች "እግዜር ያውቃል"፣ "እግዜር ስላለ ነው"፣ ወይም  "እግዜር አይፈቅድም" ማለት አጥጋቢ መልስ አይድለም። ምናልባት ለአንድ ክርስቲያን አጥጋቢ መልስ ሊሆን ይችላል። ለ 9 ሚሊዮን ሰዎች ግን አንደ መልስ ሊቆጠርም አይገባም። ለምሳሌ አንድ ኦርቶዶክስ ሐይማኖት  ተከታይ ለገና ፆም ሥጋ አለመብላት መብቱ ነው። ነገርግን የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ ሰው በመላ አብሮኝ መፆም አለበት፣ ሃይማኖቴ ሰለማይፈቅድ ስጋ ሲበላ ወይም ስጋ  መብላትን ሲደግፍ የተገኘ ይታሰር እና ኢትዮጵያዊነቱን ይነጠቅ ማለት በጭራሽ አይችልም። በተመሳሳይ መልክ ሃይማኖትን መሳሪያ አድርጎ የሰውን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ማጥቃት  ለአይምሮዬ ምንም አየገባውም። የህን ሊረዳ ማይችል ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ ካለ፣ "ከግብረ-ሶዶም የፀዳች ኢትዮጵያ!" የሚለው መዝሙር ከISIS "ከክርስትያኖች የፀዳች ዓለም" ነጠላ ዜማ ወይም ከ አዶልፍ ሂትለር "ከ አይሁድ ዘር የፀዳች ዓለም" ከተሰኘው አልበም በምን ይለያል?


1 comment:

  1. ለዚህ ፖስት አመሰግናለሁ።

    ጌይ ሰዎች ደግሞ ሰዎች ናቸው፣ ወንድ ወንድን ስለሚያፈቅር ከሴት የሚያፈቅረው ወንዶች ልዩ አይደለም። በሃይማኖት ምክንያት ብዙ ሰዎች "ጌይ መሆን መጥፎ ነው፣ ለጌዮች ሀገራችን ውስጥ ቦታ የለም" ይላሉ ግን ቦታ አለ - ጌይ ሰዎች ሁልጊዜ በዓለም ሆነዋል፣ እና ከመካከላኛ ዘመኑ በፊት ጌይ መሆን የተለመደ ነበር።

    ነገር ግን፣ ሃሳቦች እየቀየሩ ነው፣ እና ወደፊት፣ ሰው ሁሉ ተመሳሳይ መብቶች አንዳሉት ተስፋ አደርጋለሁ።

    ReplyDelete